Monday, May 11, 2026
Home Blog Page 163

በአልኮል እና በትምባሆ ላይ የሚጣለው ‘የጤና ተኮር ታክስ’ ለሕክምና አገልግሎት ድጎማ ሊውል ነው

0

የኢትዮጵያ መንግሥት በጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ለማሳደግ እና በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሕክምና ወጪ ጫና ለመቀነስ፣ በአልኮል፣ በትምባሆ እና በስኳር በበለጸጉ መጠጦች ላይ የሚጣለውን የታክስ ገቢ ለጤናው ዘርፍ ድጎማ እንዲውል ለማድረግ ማቀዱ ተገለፀ።

“ናሽናል ኸልዝ ኮምፓክት” በተሰኘው የዓለም ባንክ ሪፖርት መሰረት፣ “የኃጢአት ታክስ” (Sin Tax) ተብለው በሚጠሩት በእነዚህ ምርቶች ላይ የሚጣለው የቀረጥ ጭማሪ በቀጥታ ወደ ጤናው ዘርፍ እንዲፈስ ይደረጋል።

ከዚህ የሚገኘው ገቢ በዋነኝነት ለማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ድጎማ የሚውል ሲሆን፣ ዓላማውም አነስተኛ ገቢ ያላቸው እና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሕክምና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።

ይህ አሰራር ተግባራዊ መደረጉ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና በእጅጉ እንደሚቀንሰው ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት ታካሚዎች ለሕክምና አገልግሎት ከኪሳቸው የሚያወጡት ቀጥተኛ ወጪ 39 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፣ በመንግሥት ድጎማ እና በታክስ ገቢው ዕገዛ እ.ኤ.አ በ2030 ይህንን ወጪ ወደ 20 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ታቅዷል።

በተመሳሳይ ጊዜ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሽፋንን አሁን ካለበት 50 በመቶ ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ይህ የታክስ ገቢ እንደ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ያገለግላል።

ከገንዘብ ማሰባሰቡ ባሻገር፣ ይህ ስትራቴጂ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ የሚመድበውን በጀት ለማሳደግ ካለው ቁርጠኝነት ጋር የተያያዘ ነው።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የነበረባትን የውጭ ዕርዳታ ጥገኝነት በግማሽ በመቀነስ የሀገር ውስጥ የሀብት አሰባሰብን ለማጠናከር እየሰራች ሲሆን፣ እስከ 2030 ድረስ አጠቃላይ የጤና ወጪን 8.3 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ አልማለች።

ይህ የታክስ ማሻሻያ ውጤታማ በሆነ መንገድ ከተተገበረ፣ ለጤናው ዘርፍ ዘላቂ የገንዘብ ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ፣ ጎጂ የሆኑ ምርቶች በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ እንደ ትልቅ መፍትሔ እንደሚቆጠር ሪፖርቱ አመልክቷል።

ደቡብ ሱዳን በ2026 የአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ተተነበየ

0

የአፍሪካ ደሀና በጦርነት ክፉኛ የተጎዳችው ደቡብ ሱዳን፣ እ.ኤ.አ በ2026 የነዳጅ ምርት ወደ ቀድሞ ሁኔታው በመመለሱ ምክንያት በአህጉሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስመዘግቡ አገራትን እንደምትመራ የዓለም ባንክ አስታወቀ።

የዓለም ባንክ ባወጣው የቅርብ ጊዜው የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ መሠረት፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) በ2026 በ48.8 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ከፍተኛ ዕድገት የታቀደው አገሪቱ ባለፈው ዓመት ካጋጠማት የ23.8 በመቶ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል በኋላ መሆኑም ታውቋል።

ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማገገም የተገኘው በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆነ ሪፖርቱ ያመላክታል። የመጀመሪያው በሱዳን በኩል የሚያልፈው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ በመጠገኑ የነዳጅ ምርት ወደ መደበኛ ሁኔታው መመለሱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከአምስት ዓመታት የኢኮኖሚ ውድቀት በኋላ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መረጋጋት ነው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በበኩሉ ደቡብ ሱዳን በተጠናቀቀዉ በ2025 በ27.2 በመቶ ዕድገት እንደምታሳይ በመተንበይ የዓለም ባንክን የብሩህ ተስፋ ትንበያ አረጋግጧል። የአገሪቱ መንግሥት ገቢ ከ90 በመቶ በላይ የሚመነጨው ነዳጅ ሽያጭ እንደመሆኑ፣ የቧንቧው ጥገና ለኢኮኖሚው ትልቅ ትንፋሽ ሆኗል።

ሪፖርቱ በ2026 ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሊያስመዘግቡት የሚችሉትን ዕድገትም ይፋ አድርጓል። በዚህም መሠረት ጊኒ በ9.3 በመቶ፣ ሩዋንዳ በ7.2 በመቶ፣ ኢትዮጵያ በ7.1 በመቶ እንዲሁም ናይጄሪያ ባለፉት አሥር ዓመታት ያላየችውን ከፍተኛ ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ ተተንብዮአል።

በተቃራኒው እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ትልልቅ ኢኮኖሚዎች የ1.4 በመቶ ዝቅተኛ ዕድገት እንደሚያሳዩ ተጠቁሟል።

አዋሽ ካፒታል እና ገዳ ሴኩሪቲስ የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ የንግድ አባላት ሆኑ

0

የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አዋሽ ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አ.ማ እና ገዳ ሴኩሪቲስ ዲለርስ አ.ማ የገበያው አዲስ የንግድ አባላት ሆነው መቀላቀላቸውን በይፋ አስታወቀ።

ይህን ተከትሎ በገበያው ውስጥ ያሉትን ጠቅላላ የንግድ አባላት ቁጥር ወደ አምስት ያሳደገ ሲሆን፣ ተቋማቱ አባል መሆን የቻሉት በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሥራ ፈቃድ አግኝተው አስፈላጊውን ተቋማዊና ተግባራዊ ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑ ተጠቁሟል።

እንደ ሙሉ የንግድ አባልነታቸው፣ አዋሽ ካፒታል እና ገዳ ሴኩሪቲስ በገበያው ውስጥ የአክሲዮንና የቦንድ ግዥና ሽያጭን የማከናወን ሙሉ ሥልጣን ይኖራቸዋል። እነዚህ ተቋማት በኢንቨስተሮች እና በገበያው መካከል እንደ ድልድይ በመሆን የሚያገለግሉ ሲሆን፣ የገበያውን የገንዘብ ዝውውር በማሳለጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

የገበያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል ካሳሁን እንደገለጹት፣ የእነዚህ ተቋማት መምጣት በገበያው ውስጥ ያሉ አማራጮችን የሚያሰፋና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳር እያሳየ የመጣውን ጠንካራ እድገት የሚያመለክት ነው።

አዋሽ ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ በ200 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመ የአዋሽ ባንክ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሲሆን፣ ገዳ ሴኩሪቲስ ዲለርስ ደግሞ በጋዳ ባንክ ሥር በ80 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ወደ ሥራ የገባ የደላላና ንግድ ተቋም እንደሆነ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ 9 ኩባንያዎችን በዝርዝሩ ውስጥ ለማካተት እየሰራ ሲሆን፣ አሁን የተመዘገቡት የንግድ አባላት ኢንቨስተሮች እነዚህን ኩባንያዎች በቀላሉ እንዲያገኙና የንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አላይድ ጎልድ በመጪዉ ሚያዚያ ወር በኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ሊጀምር መሆኑ ተገለጸ

0

የካናዳው “አላይድ ጎልድ” ኩባንያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የኩርሙክ የወርቅ ማዕድን ፕሮጀክት በመጪው ሚያዝያ ወር ስራ እንደሚጀምር አስታወቀ። ኩባንያው ፕሮጀክቱ በ2026 ሶስተኛ ሩብ ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት እንደሚሸጋገር የገለጸ ሲሆን፣ በየዓመቱ 290 ሺህ አውንስ ወርቅ ለማምረት አቅዷል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፒተር ማሮን እንደገለጹት፣ ኩባንያው ለፍለጋ ስራ በየዓመቱ 8 ሚሊዮን ዶላር የመደበ ሲሆን፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ የወርቅ ክምችቱን ወደ 5 ሚሊዮን አውንስ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

ማዕድን ማውጫው ከሰፈራ መንደሮች ርቆ የሚገኝ በመሆኑ ምንም ዓይነት የህዝብ ማፈናቀል ስራ እንዳልተከናወነ የጠቀሱት ስራ አስፈጻሚው፣ ድርጅታቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች በቅድሚያ ለመቅጠር ፖሊሲ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ ምርት ሊጀምር መሆኑን ተከትሎ የአክሲዮን ዋጋው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በአራት እጥፍ በማደግ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል።

አላይድ ጎልድ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በማሊ እና በኮትዲቯር ግዙፍ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች እንዳሉት ይታወቃል።