የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚከታተለውና የሚቆጣጠረው ባለሥልጣን፣ በሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ 100 ተቋማት የንብረት ምዝገባ እንዲያካሂዱ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላለፈ። ከእነዚህም መካከል 70 የሚሆኑት የውጭ ድርጅቶች ይገኙበታል። ድርጅቶቹ ንብረታቸውን መዝግበው እንዲልኩ የተሰጠው ቀነ ገደብ እስከ ህዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ነው።
ባለሥልጣኑ ለድርጅቶቹ በላከው ደብዳቤ ላይ እንዳስረዳው፣ የንብረት ምዝገባው የሲቪል ማኅበራት በሕግ የተሰጣቸውን የንብረት ባለቤትነት መብት ሳይነካ፣ የሕዝብ ሀብት አጠቃቀም ማረጋገጫ እና የዘርፉን አጠቃላይ መረጃ ማጠናቀር የሚሉት ዓላማዎችን ለማሳካት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት፣ በሕዝብ ስም የተሰበሰበው ሀብት ለታለመለት የሕዝብ ዓላማ መዋሉን የማረጋገጥ ግዴታ በባለሥልጣኑ ላይ የሚጣል ሲሆን፣ ይህንን ግዴታ ለመወጣት የንብረት ምዝገባው ወሳኝ መሆኑን አስረድቷል።
በአገር ደረጃ በሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፍ ስር ምን ያህል የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዳለ ጥቅል መረጃ ለመያዝ፣ ለመሰብሰብና ለማጠናቀር የምዝገባው ሂደት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።


