Thursday, October 30, 2025

ኢንፊኒክስ ኢትዮጵያ ከ80 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው በተግባረ ዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የፈጠራ ማዕከል ሊመሰርት ነው ተባለ

ከ80 ዓመታት በላይ ያስቆጠረዉ አንጋፋዉ የትምህርት ተቋም የሆነዉ የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ፣ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከ 14 ዓመታት በላይ ከሆነዉ የሞባይል ስልክ አምራቹ ኢንፊኒክስ ኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ተሰምቷል።

ስምምነቱ የተፈረመው በኮሌጁ ዲን አቶ ተስፋዬ አድማሱ እና ትራንሽን ማኑፋክቸሪንግን ዳይሬክተር በአቶ ጉዎ ዦንግሌይ ሲሆን፣ ዋና ዓላማው የኮሌጁ ተማሪዎች የተግባር ላይ ልምምድ እንዲያገኙ እንዲሁም መምህራን ከአዳዲስ የኢንዱስትሪ አዝማሚያዎች ጋር ወቅታዊ የሚያደርግ የቴክኖሎጂ ስልጠና እንዲወስዱ ለማስቻል ነው ተብሏል።

በዚህ ትብብር መሰረት በኮሌጁ ኢንፊኒክስ ክለብ የሚቋቋም ሲሆን፣ ይህም ለተማሪዎች ተግባራዊ የኢንዱስትሪ ልምድ፣ የክህሎት ግንባታ እና የፈጠራ ፍለጋ እድሎችን ይፈጥራል።

በተጨማሪም ተማሪዎች በግል እና ሙያዊ እድገት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ በትራንሽን እና ኢንፊኒክስ ውስጥ የሥራ ዕድል የማግኘት ዕድል እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

የኮሌጁ ዲን “ስምምነቱ ወጣቶችን በትምህርት፣ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ለማበረታታት ያግዛል” በማለት የትብብሩን ጠቀሜታ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ፣ ይህ ትብብር የአካዳሚክ ዕውቀትን ከዘመናዊ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ልምድ ጋር በማቀናጀት ለሃገሪቱ የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ዕድገት አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።

ትራንስሽን ማኑፋክቸሪንግ በበኩሉ “ትብብሩ ለተማሪዎች የአካዳሚክ ትምህርትን ከሙያዊ ልምድ ጋር የሚያገናኙ የኢንዱስትሪ ግንዛቤዎችን፣ መመሪያዎችን እና ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ” ተስፋ ሰጥተዋል።

ኢንፊኒክስ፣ በ ትራንስሽን ማኑፋክቸሪንግ ኃ.የተ.የግ.ማ. ሥር ያለ የስማርትፎን ብራንድ ሲሆን፣ በፈጠራና በቴክኖሎጂ አማካኝነት ወጣቶችን በማብቃት ላይ እንደሚያተኩር ይታወቃል።

Related Stories