ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል ከሆኑ 24 አገራት ጋር የጉምሩክ ቀረጥ ቅናሽን በይፋ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯን ገልጻለች። ይህ እርምጃ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ ተወስዷል።
የጉምሩክ ቀረጥ ቅናሹ ሥራ ላይ የዋለው በሐምሌ 14 ቀን 2025 ዓ.ም. በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ላይ በታተመው ደንብ መሠረት ሲሆን ዓላማውም ከአፍሪካ አጋር አገራት ጋር በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ላይ ከ90% በላይ የሚሆኑ ሸቀጦች ላይ ያለውን የጉምሩክ ቀረጥ ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እንደሆነ ይታወቃል ።
የግምሩክ ኮሚሽን በቅርቡ ባስተላለፈው ሰርኩላር ደብዳቤ፣ የቀረጥ ቅናሹ የሚመለከተው ብሔራዊ መስፈርቶቻቸውን በማሟላት ለንግድ ቀጣናው ሴክሬታሪያት የንግድ ሃሳቦችን ያቀረቡትን 24 አገራት መሆኑን አሳውቋል። ከእነዚህም መካከል አልጀሪያ፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
መንግሥት ይህን ማበረታቻ ተግባራዊ ያደረገው ስምምነቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ይሁንታ ካገኘ በኋላ ነው።
መስከረም ወር 2018 መጨረሻ ላይ በይፋ ሥራ የጀመረው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣ ፤ 55 የአፍሪካ አገራትን በአንድ ወጥ ገበያ ሥር ለማዋሃድ ያለመ ነዉ። ይህ ቀጠና 1.4 ቢሊዮን ሕዝብን እና 3.4 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚሆን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርትን እንደሚያጠቃልል ተመላክቷል።






