ገቢዎች ሚኒስቴር ከ50 ሺህ ብር በላይ በሆነ ጥሬ ገንዘብ የሚፈጸሙ የንግድ ግብይቶችን በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስቴር ከሰሞኑ የሰጠውን ማብራሪያ በከፊል አግደ። በተለይም የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ማቀናነስ/ተመላሽ ጉዳይ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ “ለጊዜው ተፈጻሚ እንዳይደረግ” የሚል መመሪያ አስተላልፏል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በጥቅምት 27 ቀን 2018 ዓ.ም. ማብራሪያው፣ በገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1395/2017 የተቀመጠው ከ50 ሺህ ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ግብይት ገደብ ተፈፃሚ የሚሆነው ለገቢ ግብር ብቻ መሆኑንና የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) የግብዓት ታክስ የማቀናነስ መብትን እንደማይገድብ በዝርዝር አስቀምጦ ነበር።
በተጨማሪም፣ ገዥዎች ከገደቡ በላይ በጥሬ ገንዘብ ከከፈሉ፣ ትርፍ ግብር በሚሰላበት ጊዜ ትርፍ ክፍያው እንደተቀናሽ ወጪ እንደማይያዝ እንዲሁም ሻጮችም ከገደቡ በላይ ጥሬ ገንዘብ ከተቀበሉ እኩል የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።ሆኖም የገቢዎች ሚኒስቴር በጥቅምት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ባስተላለፈው የሰርኩላር ደብዳቤ ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር የሰጠው የቫት ማቀናነስ ማብራሪያ አዋጁ የተፈለገበትን “የታክስ ስወራ ድርጊት ለማስቀረት” የሚለውን ዓላማ “በአግባቡ ያልተመለከተ” በመሆኑ ውይይት እንዲደረግበት በመግለፅ ” የቫት ማቀናነስ/ተመላሽ ጉዳይ ለጊዜው ተፈጻሚ እንዳይደረግ አዟል።
በገቢ ግብር አዋጁ ላይ የተቀመጡት ሌሎች የጥሬ ገንዘብ ገደቦች፣ በተለይም ገዥዎች የተቀናሽ ወጪ መብታቸውን የሚያጡበት እና ሻጮች ቅጣት የሚጣልባቸው ድንጋጌዎች፣ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ሚኒስትሩ አስታውቋል።በተጨማሪም፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ገቢ ወይም ሽያጭ የለንም በማለት ባዶ የሚያሳውቁ ታክስ ከፋዮችን አነስተኛ አማራጭ ግብር ለማስከፈል የሚያስችል ዝርዝር ማብራሪያ ከገንዘብ ሚኒስቴር እስኪመጣ ድረስ፣ ቀደም ሲል በተሰጠው አሰራር እንዲስተናገዱ ማዘዙን ለካፒታል የደረሰው የአፈፃፀም መመሪያው ያመለክታል።






