የዓለማችን ግዙፍ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ኩባንያ ካርፉር በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት የሚያስችለውን የቢዝነስ ሞዴል በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገለጸ።
የካርፉር ኮሜርሻል ዳይሬክተር የሆኑት ጄሮሜ ቦንዚ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሰማራት የሚያስችል የቢዝነስ ሞዴል እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን ዕቅድ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ቡድን በቅርብ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ አስታውቀዋል።
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን ከኩባንያው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።
በውይይቱ ላይ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ባደረገቻቸው አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎችና ያሉ አማራጮችን አስረድተዋል የተባለ ሲሆን ድርጅቱ በበኩሉ ደግሞ የኢትዮጵያን ገበያ ለረጅም ጊዜ ሲከታተለው እንደነበርና ፣ መንግስት የውጪና ገቢ ንግድ ሴክተሩን ለውጭ ባለሀብቶች መክፈቱ ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው አስረድቷል።
በፈረንጆቹ በ1959 በፈረንሳይ የተመሰረተው ካርፉር በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ በሚገኙ መሸጫ ማዕከላቱ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን የሚያስተናግድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው።





