በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (ኢትዮጵያ ቻምበር) እና በአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) መካከል በሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የንግድ ምክር ቤቶች ሕንፃ ላይ በቀረበው የይገባኛል ውዝግብ ላይ፣ የቂርቆስ ምድብ 1ኛ ፍ/ብሄር ችሎት የእግድ ዉሳኔ አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት በሰጠው ውሳኔ መሰረት፣ ኢትዮጵያ ቻምበር ቀደም ሲል ይዞ የነበረውን የቢሮ ክፍል በአስቸኳይ ለአዲስ ቻምበር እንዲያስረክብ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ የሰጠው፣ ኢትዮጵያ ቻምበር ቀደም ሲል የፍርድ ቤቱን ብይን በመጣስ፣ አዲስ ቻምበር ይዟቸው የነበሩ ክፍሎችን በኃይል እንደያዘ አዲስ ቻምበር ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ነው።

ፍርድ ቤቱ ህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ባሳለፈው ብይን፣ ተከሳሽ (ኢትዮጵያ ቻምበር) ሕንጻውን ለልማት ከማዋሉ በፊት ለአዲስ ቻምበር ምትክ ክፍሎችን አስቀድሞ ማዘጋጀትና ለፍርድ ቤቱ ማሳወቅ እንደነበረበት አመልክቶ ነበር።
የኢትዮጵያ ቻምበር ይህንን ትዕዛዝ በመጣስ የክፍሎቹን ቁልፎች ሰብሮ መግባቱ በአዲስ ቻምበር በኩል መገለጹን ተከትሎ፣ ፍርድ ቤቱ ኢትዮጵያ ቻምበር ክፍሎቹን በአስቸኳይ ለከሳሽ (አዲስ ቻምበር) እንዲያስረክብ በድጋሚ በጥብቅ አዟል።
የካፒታል ዘገባ የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፣ ቁጥራቸው 20 ገደማ የሆኑ የኢትዮጵያ ቻምበር ሰራተኞች የቢሮውን ግድግዳና በር በመስበር ንብረቶችን ወደ ውጪ ሲጥሉ ነበር።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው፣ “በፍርድ ቤቱ ተጥሎ የነበረውን የማልማት እግድ ትላንት (ህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም.) በማንሳቱ ነው ዛሬ (ህዳር 2 ቀን 2018) ወደ ተግባር የገባነው” ሲሉ ለካፒታል ገልፀው ነበር። የንግድ ምክር ቤቶች ሕንፃ ውዝግብ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያመለክታል።




