የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ አህጉሪቱ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት “ፍትህ እንጂ ልመና አትጠይቅም” በማለት፣ G20 የዓለምን የፋይናንስ መዋቅር ስር ነቀል ለውጥ እንዲያደርግ ጠንካራ ጥሪ አቀረቡ።
የአፍሪካ ሕዝብ ዕዳ 1.8 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ በ2024 ብቻ ከ70 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለዕዳ አገልግሎት ተከፍሏል። ይህ ከፍተኛ ክፍያ የካፒታል ወጪያችን ከሌሎች አገሮች በሁለት እጥፍ በላይ በመሆኑ የሚጣለው “በልማት ላይ የሚፈጠረዉ የግብር ስወራ” ነፀብራቅ እንደሆነ ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል።
በዚህ አድልዎ ምክንያት 57 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ ለሰብአዊ ልማት ከሚውለው የማህበራዊ ወጪ በላይ ለዕዳ አገልግሎት በሚከፈልባቸው አገሮች ውስጥ ይኖራል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ የፋይናንስ ሉዓላዊነቱን ለመገንባት እና በሥርዓቱ ውስጥ ያለውን አድልዎ ለመጋፈጥ፣ G20 “አዲስ የፋይናንስ ስምምነት” እንዲመሠርት ጠይቋል።
በተጨማሪም አፍሪካ የፋይናንስ ሉዓላዊነቷን ለማጠናከር የዕዳ ቁጥጥር ዘዴ እና የብድር ደረጃ አሰጣጥ ኤጀንሲን የመሰሉ የራሷን ተነሳሽነቶች በማዘጋጀት ላይ መሆኗን አስታውቀው፣ ዉይይቱ”ስለ ክብር፣ ልማት እና ዕጣ ፈንታ” በመሆኑ አፍሪካ “እኩል አጋር” ሆና ቦታዋን የምትመልስበት ነው በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።




