የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ላይ የታየውን የዋጋ መናር ለመቆጣጠር እየወሰደ በሚገኘዉ እርምጃ፣ ዛሬ ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም. በባንኮች በኩል የሚሸጠው የዶላር ዋጋ 155.05 ብር መድረሱ ታውቋል። ይህ እርምጃ የመጣው በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ እስከ 190 ብር አሻቅቦ በነበረበት ወቅት ነው።
የዶላር ፍላጎቱ ድንገት የጨመረው በቻይና አዲስ ዓመት ምክንያት ነው። የካቲት ወር ላይ በቻይና ፋብሪካዎችና ወደቦች ሥራ ስለሚያቆሙ፣ ኢትዮጵያውያን አስመጪዎች እስከ ሚያዝያና ግንቦት የሚበቃቸውን ዕቃ አሁኑኑ ለማዘዝ ዶላር ፍለጋ ወደ ገበያው ጎርፈዋል። ይህ ግፊት በጥቁር ገበያው ላይ ትልቅ የዋጋ ንረት ፈጥሮ ነበር።
ይህንን የፍላጎት ግፊት ለመቀነስ ባንኩ ባለፈው ሳምንት (ጥር 19) ሪከርድ የሆነ የ500 ሚሊዮን ዶላር ልዩ ጨረታ በማካሄድ ባንኮች የአስመጪዎችን ፍላጎት እንዲያሟሉ አድርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ ንኮች የብድር ሰነድ (LC) ሲከፍቱ የጉምሩክ ኮሚሽንን የዋጋ መረጃ እንዲጠቀሙ ታዘዋል። ይህም አስመጪዎች ዕቃዎችን ከትክክለኛ ዋጋቸው በታች በማስመዝገብ በሕገ-ወጥ መንገድ ዶላር እንዳያወጡ ይከለክላል።
ዛሬ ማክሰኞ ጥር 26፤2018 ዓ.ም. በተካሄደው 17ኛው ዙር ጨረታ፣ ባንኩ 70 ሚሊዮን ዶላር ለገበያ መቅረብ ይታወቃል። በዛሬዉ ጨረታው የታየው የ155.05 ብር ተመን ከባለፈው ሳምንት የ23 ሳንቲም ጭማሪ አሳይቷል።
በዚህ ጨረታ በባንኮች በኩል የቀረበው የፍላጎት መጠን 127.25 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ፣ አቅርቦቱና ፍላጎቱ ባለመመጣጠኑ ምክንያት በባንኮች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ተፈጥሯል።
በዚህም ምክንያት በጨረታው ከተሳተፉ 19 ባንኮች መካከል ዶላር ማግኘት የቻሉት 8 ባንኮች ብቻ ሲሆኑ በጨረታው የቀረበው ዝቅተኛው የመግዣ ዋጋ ደግሞ 154.8141 ብር ሆኖ ተመዝግቧል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ብሔራዊ ባንክ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ወደ 890 ሚሊዮን ዶላር ለገበያ ማቅረቡ በጥቁር ገበያና በባንክ መካከል ያለውን ልዩነት እያጠበበው ይሄዳል። የዛሬው ጨረታ ዋጋ መጨመርም፣ ገበያው ወደ ትክክለኛ የዋጋ ግኝት እየሄደ መሆኑን ያሳያል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አለምአቀፍ የገንዘብ ድርጅት ( አይኤምኤፍ) ከሰሞኑ ባወጣዉ ሪፖርት በባንኮች እና በትይዩ ገበያ (ጥቁር ገበያ) መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ወደ 13 በመቶ ከፍ ብሏል።
በዚህም ከመስከረም እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በይፋዊው የባንክ ተመን እና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት ከ10 በመቶ በታች ወርዶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ልዩነቱ በድጋሚ እያገረሸ መምጣቱን ተመላክቷል።
ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የተቀመጠው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬን ከጨረታ ውጭ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሸጡ ነዉ ያለዉ ድርጅቱ ይህም የምንዛሬ ተመኑ በገበያ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ የፍላጎት እና የአቅርቦት ሁኔታ እንዳያንጸባርቅ አድርጎታል።
በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ በሚያካሂደው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ላይ ባንኮች ሊያገኙ የሚችሉት ድርሻ ላይ ገደብ መቀመጡ፣ ባንኮች ያላቸውን የምንዛሬ ፍላጎት በነፃነት እንዳያሟሉ እና ትክክለኛ የዋጋ ግኝት እንዳይኖር እንቅፋት መሆኑን አይኤምኤፍ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ ገበያ መር የምንዛሬ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ፣ እንዲህ ያሉ ጨረታዎችን ማካሄዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍና ለንግድ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረትን ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ገልጿል። ባንኩ በቀጣይም በተያዘለት መርሃ ግብር መሠረት የውጭ ምንዛሬ ሽያጩን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በኢያሱ ዘካሪያስ





