ትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ የትምህርት ተቋማት የሚመሩበትን አዲስ ረቂቅ ደንብ ማዘጋጀቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ረቂቁ በተለይ በውጭ ሀገር ማኅበረሰቦች ለሚቋቋሙ ትምህርት ቤቶች አስገዳጅ መስፈርቶችን አኑሯል።
ካፒታል የተመለከተዉ ረቂቅ ደንቡ እንደሚያስገድደው፣ በውጭ ሀገር ማኅበረሰብ የተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ከጠቅላላ በጀታቸው ውስጥ 30% (ሰላሳ በመቶ) የሚሆነው ከሀገራቸው መንግሥት ድጋፍ ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ቀሪውን 70% ደግሞ ራሳቸው መሸፈን የሚችሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ግዴታ ተጥሏል።
ይህ የፋይናንስ ማረጋገጫ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና አግባብ ባለው የሰነዶች ማረጋገጫ ባለሥልጣን ተረጋግጦ መቅረብ እንዳለበት ደንቡ ያመለክታል። ሚኒስቴሩ ይህን መስፈርት ያኖረው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የፋይናንስ መረጋጋትና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ ይጠበቃል።
በዚህ ለትምህርት ማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት አስተያየት ክፍት በተደረገዉ አዱሱ ረቂቅ ደንብ፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ የትምህርት ተቋማት የአገሪቱን የትምህርት ሕግ፣ የመምህራን ብቃት፣ የተማሪዎች መብት እና የትምህርት ደረጃን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ሕጎችን ማክበር ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ደንብ ላይ እንደተገለፀዉ ፤ተቋማቱ የራሳቸው የሆነ የገንዘብ ምንጭ (ከተማሪዎች ክፍያ፣ ከስጦታ ወይም ከኢንቨስትመንት ትርፍ) እና ነጻ አስተዳደር ያለው ድርጅታዊ አወቃቀር ሊኖራቸው ይገባል።
ረቂቅ ደንብ ላይ ሚኒስቴሩ ተቋማት ሊያስከፍሉት የሚችሉትን የትምህርትና ሌሎች አገልግሎት ክፍያዎችን ጣሪያ በተመለከተ መመሪያ እንደሚያወጣና በየሦስት ዓመቱ እንደሚስተካከል ደንግጓል። የክፍያ ጭማሪ ለማድረግ ከ3 ወራት በፊት ተጠቃሚዎችን ማወያየት እንደሚኖርባቸው ያስገድዳል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ የአጠቃላይ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴሩ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደገና መመዝገብ እንዳለባቸው የተገለፀ ሲሆን ተቋማት የልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና ተማሪዎቻቸው ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የትምህርት የምክር አገልግሎት ማግኘታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስታዉቋል።
ትምህርት ሚኒስትሩ አዲሱ ደንብ የመንግሥታዊ ያልሆኑ ትምህርት ተቋማትን ምዝገባ፣ ዕውቅና እና ቁጥጥር በአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1368/2017 መሠረት የሚያከናውን መሆኑን በግልጽ አስረድቷል።






