የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ፍላይዱባይ (FlyDubai) ወደ ሶማሊላንድ ለሚደረጉ በረራዎች የጉዞ መመሪያዎቻቸውን በማዘመን፣ የሶማሊያ የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ (ኢ-ቪዛ) መስፈርት በሃርጌሳ እና በበርበራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ እንደማይሠራ በይፋ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳስታወቀው “የሶማሊያ የኢ-ቪዛ መስፈርቶች ወደ በርበራ ወይም ሃርጌሳ ለሚመጡ ተሳፋሪዎች አይሰራም” በማለት ገልጿል። አየር መንገዱ ወደ ሶማሊላንድ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ሲደርሱ ቪዛ ማግኘት እንደሚችሉ አፅንኦት ሰጥቷል።
ፍላይዱባይ በተመሳሳይ የጉዞ ማስጠንቀቂያውን በማሻሻል፣ መንገደኞች በሃርጌሳ እና በበርበራ ሲደርሱ ቪዛ ማግኘት እንደሚችሉ አረጋግጧል። ይህ እርምጃ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA)ን ጨምሮ በርካታ አካላት የሶማሊላንድን የኢሚግሬሽን ቁጥጥር ከሶማሊያ ሥርዓት በመለየት የጉዞ መመሪያዎችን ካወጡ በኋላ የተወሰደ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የአየር መንገዶቹ መመሪያዎች መሻሻል የተከሰተው ዩናይትድ ስቴትስ በሶማሊያ የኢ-ቪዛ ሲስተም ላይ ትልቅ የደኅንነት ጥሰት ከተፈጸመ በኋላ ባወጣችዉ አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ ነዉ።
በሶማሊያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዳረጋገጠው፣ ጠላፊዎች የሶማሊያን የኢ-ቪዛ መድረክ ሰብረው በመግባት ቢያንስ የ35,000 አመልካቾችን የግል መረጃ ተጋልጧል።
ከዚህ ከተጋለጡት መረጃዎች መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ዜጎችን ጨምሮ ስም፣ የፓስፖርት ፎቶዎች፣ የትውልድ ቀኖች፣ የኢሜይል አድራሻዎች እና የመኖሪያ አድራሻዎች ይገኙበታል ተብሏል።
የአሜሪካ መንግሥት የሶማሊያን ኢ-ቪዛ ሲስተም የተጠቀሙ ዜጎቹን በአስቸኳይ በአቅራቢያቸው የሚገኘውን ኤምባሲያቸውን እንዲያነጋግሩ እና ማንኛውንም አጠራጣሪ እንቅስቃሴ እንዲከታተሉ አሳስቧል።
ባለሞያዎች እንደሚሉት፣ በሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እና በሱማሊላንድ መንግስት መካከል በአቪዬሽን ቁጥጥር ዙሪያ የሚታየው ውጥረት በሁለቱ አካላት ስልጣን ላይ የሚደረግ የፖለቲካ ትግል ማሳያ ነው።
ለዚህ ዉጥረት መነሻዉ የሶማሊያ አቋም መላውን የአየር ክልል የመቆጣጠር ስልጣን የእኔ ነው የሚል ሲሆን፣ ይህንንም ለማስፈጸም ወደ ሀርጌሳ ለሚጓዙ ሁሉም ተሳፋሪዎች የሶማሊያ ኢ-ቪዛ እንዲኖራቸው አዟል። በሌላ በኩል፣ የሶማሊላንድ አቋም ደግሞ ራሷን የቻለች ሀገር በመሆኗ የአየር ክልሏን በሙሉ የመቆጣጠር መብት እንዳላት ትናገራለች።
በዚህ መሠረት፣ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በሰማሊላንድ አየር ማረፊያዎች (እንደ ሀርጌሳ) ከማረፋቸው በፊት ከራሱ የክልል ባለሥልጣናት የቅድሚያ ፈቃድ እንዲያገኙ በማዘዝ፣ የሶማሊያን ኢ-ቪዛ ሕገ-ወጥ መሆኑን በመቃወም በአንድ ክልል ላይ የቁጥጥር ስልጣንን ለመጠየቅ የሚያደርጉትን ጥረት በተግባር እያሳዩ መሆኑ ተመላክቷል።





