በትግራይ ክልል ውስጥ ከሁለት ዓመታት የእርስ በርስ ግጭት በኋላ፣ በዓለም አቀፍ ላይ የሚስተዋለዉን የወርቅ ዋጋ መናር ተከትሎ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅስ ሕገ-ወጥ የወርቅ ንግድ መፋፋሙን አዲስ የጋራ ምርመራ አመለከተ።
ምርመራው እንደሚያመለክተው፣ የካናዳው ኩባንያ ኢስት አፍሪካ ሜታልስ ንብረት በሆኑት ማቶ ቡላ እና ዳ ታምቡክ ማዕድን ቦታዎች ላይ ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት ተግባር በስፋት እየተፈጸመ ነው።
ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ከ ቡሮ ኦፍ ኢንቨስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ጋር ባደረጉት ምርመራ መሠረት፣ ሥራ ያልጀመሩና ተደራሽ አይደሉም የተባሉት እነዚህ ቦታዎች ላይ፣ የቀድሞ ወታደሮች እና የቻይና ማዕድን ቆፋሪዎች ስማቸው ያልተገለጸ ባለሀብቶች ድጋፍ አግኝተው ከ2024 መጀመሪያ አንስቶ እስከ 2025 አጋማሽ ድረስ ወርቅ ሲያወጡ ቆይተዋል።
ሪፖርቱ በክልሉ ከጦርነቱ በኋላ በተፈጠረው የፖለቲካ ክፍተት ሳቢያ ያልተገደበ የማዕድን ማውጣት ኢኮኖሚ መጧጧፉን ያሳያል። ወታደራዊ ቡድኖች እና የአካባቢ አዛዦች ቁልፍ የማዕድን ክምችቶችንና የኮንትሮባንድ መንገዶችን በመቆጣጠር፣ ሕገወጥ ቁፋሮው እንዲስፋፋና የክልሉ ሀብት በቁጥጥር ስር በሌለ መንገድ እንዲባክን ምክንያት ሆነዋል።
የወርቅ ዋጋ በዓለም ገበያ በዚህ ዓመት ብቻ ከ50% በላይ መጨመሩ ዋናው ማነቃቂያ ሲሆን፣ ክልሉ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ሳይረጋገጥ ወደ “ሱዳን መሰል የሀብት ግጭት” ሊያመራ የሚችል አደጋ ተጋርጦበታል ተብሏል።
የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ሕገወጥ ተግባሩን ለማስቆም እና ንብረቶችን ለመያዝ ግብረ ኃይል ቢሰማሩም፣ በደቡባዊው የክልሉ ክፍል እየተባባሰ ያለው ግጭት የማስፈጸም ስራውን አደጋ ላይ እየጣለው መሆኑ ተገልጿል።
በ2017 በጀት ዓመት 10 ወራት ብቻ ከትግራይ ክልል ለብሔራዊ ባንክ ከ12 ሺህ 210 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ከሌሎች ክልሎች የሚበልጥ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።
የቫንኩቨሩ ኩባንያ ኢስት አፍሪካ ሜታልስ፣ ሁለቱን ፕሮጀክቶች ለማልማት ከቻይናው ቲቤት ሁዋዩ ማይኒንግ ጋር እንደሚሰራ አስታውቋል። የቻይናው አጋር ፕሮጀክቶቹ ሙሉ ፍቃድ ያላቸው መሆናቸውንና ለምርት ዝግጁ እስኪሆኑ ድረስ 100% የልማት ወጪዎችን እንደሚሸፍን ኩባንያው ገልጿል።
ይሁን እንጂ፣ ኢስት አፍሪካ ሜታልስ በየትኛውም ሕገወጥ ተግባር ውስጥ እንዳልተሳተፈ በመግለጽ፣ የቻይና አጋሮቹም ሕገወጥ ቁፋሮዎችን ፈጽመዋል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጓል። ሆኖም ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ከሲልክ ሮድ ኢንቨስትመንትስ እና ከትግራይ ሪሶርስስ ጋር ግንኙነት ያላቸው የቻይና ቡድኖች በእነዚህ ቦታዎች ላይ ወርቅ ሲያወጡ መቆየታቸውን አመልክተዋል።





