ሳፋሪኮም ቴሌኮሙኒኬሽንስ ኢትዮጵያ ኃ.የተ.የግ.ማ.፣ የኩባንያውን የአድቫይዘሪ ቦርድ ሊቀመንበርነት ቦታ ለአዲስ መሪ መስጠቱን አስታውቋል። የግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ (GPE) ቦርድ አቶ ኤርሚያስ እሸቱን ቀደም ሲል የቦርዱን ሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩትን ፒተር ንዴግዋን በመተካት፣ ከህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የአድቫይዘሪ ቦርድ ሊቀመንበር አድርጎ ሾሟል።
ይህ ሹመት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለአካባቢያዊ አመራር (localization) እና ለኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የአመራር ሚናዎች ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለሚያደርገው ጥረት ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ተገልጿል።
አቶ ኤርሚያስ ከመጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የአድቫይዘሪ ቦርድን የተቀላቀሉ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አባል ነበሩ። አሁን ወደ ሊቀመንበርነት ማደጋቸው የኩባንያው በአገር ውስጥ አመራር ላይ ያለውን እምነት ያጎላል ተብሏል።
በአዲሱ ኃላፊነታቸውም ቦርዱ ውጤታማ ሆኖ እንዲሠራ መምራትና ማስተባበር፣ እንዲሁም ኩባንያውን በውጭ ግንኙነት መወከል ይጠበቅባቸዋል።
የGPE ቦርድ ሊቀመንበር እና የሳፋሪኮም ኃ.የተ.የግ.ማ. ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ፒተር ንዴግዋ በሰጡት አስተያየት፡- “የእርሳቸው (የኤርሚያስ) በፋይናንስ፣ በአስተዳደር እና በተቋማዊ ለውጥ ላይ ያለው ሰፊ ልምድ፣ ከገበያው ጥልቅ ግንዛቤ ጋር ተዳምሮ ኩባንያውን ወደ ቀጣዩ የዕድገት ምዕራፍ ለመምራት ያስችላቸዋል።” ብለዋል
።
ፒተር ንዴግዋ ከመጋቢት 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ቦርድ እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የአድቫይዘሪ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ግን በGPE ቦርድ ሊቀመንበርነት ብቻ ይቀጥላሉ።
GPE ቦርድ ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት፣ ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን፣ ቮዳኮም፣ ቮዳፎን፣ ሳፋሪኮም ኃ.የተ.የግ.ማ. እና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን የተሰኙ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያካትታል።
አቶ ኤርሚያስ እሸቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዘመናዊነት እና የግል ዘርፍ ዕድገት በማስፋፋት የሚታወቁ፣ በንግድ አስተዳደር፣ በፋይናንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱ መሪ መሆናቸው ተመላክቷል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን የኢትዮጵያን የመጀመሪያውን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት መድረክ የጀመሩ ሲሆን፣ ዘመን ባንክን ከመሰረቱት እና በኋላም ሊቀመንበር ከሆኑት መካከል አንዱ ናቸው።
በአቶ ኤርሚያስ አመራር ስር የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቦርድ ህግ አስተዳደርን በማጠናከር፣ የስራ ዕድል በመፍጠር እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የድርጅት አሰራርን በመትከል በኢትዮጵያ አሳታፊ ዲጂታል-ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት ትኩረት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።





