በኢትዮጵያ የሥጋ ኤክስፖርት ዘርፍ ውስጥ ለዓመታት እንቅፋት ሆኖ የቆየውና ላኪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ የነበረው የታክስ አወሳሰን ሥርዓት መሠረታዊ ለውጥ እንደተደረገበት ተገልጿል።
የገቢዎች ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጡት አዲስ መመሪያ መሠረት፣ ቀደም ሲል የሥጋ ላኪዎች ከቁም እንስሳት አቅራቢዎች ጋር በሚያደርጉት ግብይት ላይ ሕጋዊ ደረሰኝ ማቅረብ ባለመቻላቸው ምክንያት ይጣልባቸው የነበረው የ35 በመቶ የንግድ ትርፍ ግብር ውሳኔ እንዲቀየር ተደርጓል።
በኢትዮጵያ የቁም እንስሳት አቅርቦት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ያልተከተለ በመሆኑ፣ ኤክስፖርት ቄራዎች እንስሳትን ከአርብቶ አደሮችና ከአነስተኛ አቅራቢዎች በሚገዙበት ወቅት ሕጋዊ ደረሰኝ ማግኘት ሲሳናቸው ቆይቷል።
ላኪዎቹ ግብይቱን በግዥ ማረጋገጫ ለመፈጸም ቢሞክሩም፣ አብዛኞቹ ሻጮች ለዚህ ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና የታክስ ሕጉም በአንድ ሻጭ በዓመት ከ500 ሺህ ብር በላይ ግብይት ሲፈጸም ደረሰኝ ግዴታ መሆኑን በመደንገጉ፣ የታክስ ባለሥልጣኑ ላኪዎች ያወጡትን ወጪ ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ላኪዎች ክፍያው በባንክ የተፈጸመ መሆኑን ቢያሳዩም፣ የታክስ ባለሥልጣኑ የወጪውን 65 በመቶ ብቻ በመቀበል፣ በቀሪው 35 በመቶ ላይ የንግድ ትርፍ ግብር ውሳኔ ያስተላልፍ ነበር። ይህ አሠራር ላኪዎች ሊከፍሉት የማይችሉት የታክስ ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁና አንዳንዶቹም ከሥራቸው እንዲደናቀፉ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ካፒታል መዘገቡ ይታወሳል።
ይህ ችግር ሀገሪቱ ከሥጋ ኤክስፖርት ልታገኝ የምትችለውን የውጭ ምንዛሪ በማዳከሙና አዳዲስ ገበያዎችን የማስፋፋት ሥራውን በማደናቀፉ፣ ብሔራዊ የኢንዱስትሪ ካውንስል ጉዳዩ ተጠንቶ መፍትሔ እንዲሰጠው አቅጣጫ አስቀምጧል።
በዚህም መሠረት ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን የተውጣጣ የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ችግሩን መመርመሩ ተጠቁሟል።
ጥናቱ እንደጠቆመው፣ ላኪዎች ላይ የሚጣለው 35 በመቶ የታክስ ዕዳ ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል። ይህንን ስጋት ለማቃለልም ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበው ጸድቀዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የተላለፈው ውሳኔ እንደሚያሳየው፣ የቁም እንስሳት አቅራቢዎች ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ተፈጻሚ እስኪሆን ድረስ አዲስ አሠራር ሥራ ላይ ውሏል። አዲሱ መመሪያ ላኪዎች ከአቅራቢዎች በሚፈጽሙት ግዥ ላይ የ3 በመቶ ቅድመ ግብር (Withholding Tax) ቀንሰው ለታክስ ባለሥልጣኑ ገቢ እንዲያደርጉ ያዝዛል።
ይህ የቅድመ ግብር አሠራር ቀደም ሲል በነበረው መመሪያ ቁጥር 2/2011 መሠረት ላኪዎች ላይ ተፈጻሚ ባይሆንም፣ አሁን ግን በዘርፉ የታየውን የደረሰኝ ችግር ለመፍታት ሲባል በልዩ ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን ተወስኗል።
በመመሪያው መሠረት ወጪው ተቀባይ እንዲሆን ለቁም እንስሳት አቅራቢው የተከፈለው ክፍያ በባንክ የተፈጸመ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ መቅረብ ያለበት ሲሆን፣ የግዥው መጠንና ዋጋም በግብርና ሚኒስቴር (በእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት) ተጠንቶ ከጸደቀው ስታንዳርድና ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ጋር መነጻጸር ይኖርበታል።
በተጨማሪም ምርቱ ወደ ውጭ ተልኮ የውጭ ምንዛሪ የተገኘበት መሆኑ መረጋገጥና አቅራቢውም የጸና የንግድ ፈቃድ ያለው ሊሆን ይገባል።
ይህ አሠራር እስከ አሁን የታክስ ውሳኔ ላልወጣባቸው ጉዳዮችና ወደፊት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እስኪዘረጋ ድረስ እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ የሚያገለግል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ፣ ለመካከለኛና ለክልል የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተሰራጭቶ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሔው በእንስሳት ዝርያዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የአቅርቦትና የዋጋ መረጃን በቴክኖሎጂ የታገዘ የማሰባሰብ ሥራ መሥራት መሆኑ ተጠቁሟል። አዲሱ መመሪያ በኤክስፖርት ቄራዎች ላይ የነበረውን የታክስ ስጋት በመቅረፍ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢያሱ ዘካሪያስ





