የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገኘው አንቴክስ ቴክስታይል ድርጅት ጋር በተያያዘ መግለጫ አዉጥቷል። ኮንፌዴሬሽኑ ለካፒታል በላከዉ ማስተባበያ፣ ድርጅቱ በውስጡ በሠራተኞች ላይ የተፈጸመውን ሕገ-ወጥ ድርጊት ከአስተዳደራዊ ኃላፊነት ለመሸሽና ድርጊት ፈጻሚውን ለመደገፍ ሆን ተብሎ የተዘጋጀ መግለጫ አሰራጭቷል ሲል ከሷል።
ጳጉሜ 3 ቀን 2018 ዓ.ም በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንቴክስ ቴክስታይል ድርጅት ማደሪያ (ዶርም) ውስጥ በቻይናዊው ዣንግ ጃሂ እና በኢትዮጵያዊው ወርቅነህ ጀማነህ መካከል የጸረ-ተባይ ርጭት ሽግሽግን ባለመፈጸም ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።
ድርጅቱ ጉዳዩን ተከትሎ ዣንግ ጃሂን ከሥራ በማገድ ለሕግ አሳልፎ መስጠቱን እና ጉዳት ደርሶበታል የተባለው ወርቅነህም የሕክምና ምርመራ ተደርጎለት ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም የተሰበረ ስልኩ ተተክቶለትና በጠየቀው መሠረት የሞራል እና የገንዘብ ካሳ ተከፍሎ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መፈታቱን መግለጹ የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ኢሰማኮ ይህንን ማስተባበያ አጥብቆ ተቃውሟል። በድርጅቱ ውስጥ በሠራተኞች ላይ ውሻ በመልቀቅና ኬሚካል በመርጨት አምስት ሠራተኞች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተው መታከማቸውን የጠቀሰው ኮንፌዴሬሽኑ፣ ድርጅቱ ይህንን አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ጥሰት ችላ በማለትና ከኃላፊነት ለመሸሽ ሲል ሠራተኞች በራሳቸው ማደሪያ በሩን ለመክፈት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በሩን ሰብሮ ለመግባት ተገዷል የሚል የተሳሳተ ትርክት እየገነባ ይገኛል ብሏል።
ኢሰማኮ አክሎም፣ ጥፋተኛው አካል በድርጅቱ በኩል በይፋ ተቀጥሮ የገባ ሠራተኛ መሆኑን ጠቅሶ፣ ድርጅቱ የተፈጸመውን ሕገ-ወጥ ድርጊት አቅጣጫ በማሳትና አጥፊውን ነጻ ለማውጣት የሚያስችሉ ማስረጃዎችን እያዘጋጀ ነው ሲል አጣጥሎታል። ይህን ተከትሎ ድርጅቱ ራሱን ከኃላፊነት ነፃ ለማድረግ የሚያወጣውን መግለጫ እንደማቀበለው ያስታወቀው ኮንፌዴሬሽኑ፣ የሠራተኞችን ሰብአዊ ክብር ለማስጠበቅና ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስቧል።






