የአለም ባንክ እና የሮክፌለር ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ጨምሮ በስድስት የአፍሪካ ሀገራት የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ለተቀረጸው ፕሮጀክት የ50 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ይህ በዋሽንግተን ዲሲ መቀመጫውን ባደረገው “ክላስፕ” በተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የሚመራው ፕሮጀክት፤ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የግብርና መሣሪያዎች ለገበሬዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ለማድረግ ያለመ ነው።
ፕሮጀክቱ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የምርት ማከማቻ ቅዝቃዜ ክፍሎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣ የውሃ ፓምፖች፣ የእህል ወፍጮዎች እና ሌሎች ምርታማነትን የሚጨምሩ መሣሪያዎች ላይ ነው።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ዩጋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን፣ አቅራቢዎችና አከፋፋዮች መሣሪያዎቹን በዝቅተኛ ዋጋ ለገበሬው እንዲያቀርቡ የገንዘብ ድጎማና የቴክኒክ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይልና የማቀዝቀዣ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ምክንያት ገበሬዎች ከሚያመርቱት ምርት ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚሆነው እንደሚባክን ይገመታል።
ይህ ድጋፍ የአለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ በጋራ የቀረጹት የ”ሚሽን 300″ አካል ሲሆን ዕቅዱ እ.ኤ.አ በ2030 ለ300 ሚሊዮን አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ600 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማያገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።






